በዲላ ዩኒቨርሲቲ የ2015 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች የሞዴል ፈተና መሰጠት ተጀመረ

ዲ.ዩ፦ ግንቦት 09/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለ2015 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በ"ኦንላይን" የታገዘና ለአገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና የሚያዘጋጅ የሞዴል ፈተና መስጠት ጀምሯል።
ማቴዎስ ሀብቴ (ዶ/ር)፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ፤ በመጪው ሐምሌ ወር በመንግስትና የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ ይሰጣል ተብሎ እቅድ የተያዘለትን የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና በዩኒቨርሲቲው በብቃት ለመስጠት ሰፊ ዝግጅት ሲደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ከነዚህም መካከል የመውጫ ፈተናን ለመተግበር የሚያስችል የ"ኦንላይን" ፈተና አስተዳደር ስርዓት ማበልፀግ አንዱ እንደነበር አስታውሰው፤ በዛሬው ዕለትም በዩኒቨርሲቲው ለ2015 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በበይነ መረብ የሞዴል የሙከራ ፈተናን በ"ኦንላይን" መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።
እንደ ዶ/ር ማቴዎስ ሀብቴ ገለፃ፤ በመጪው ሐምሌ ወር በዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ዙር ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎች 1882 ሲሆኑ፤ ለነዚህም ከውጭ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመጡ ተፈታኝ ተማሪዎች ካሉም ታሳቢ በማድረግ ለፈተናው 540 ኮምፒተሮች ዝግጁ
መደረጋቸውን ገልጸዋል።
የሞዴል ፈተናው ከዛሬ ግንቦት 9/2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት በዩኒርሲቲው ነባሩ ግቢ እና ኦዳያኣ ግቢ ይሰጣል። በስምንት ኮሌጆች ስር ያሉ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እና መምህራን በተዘጋጀላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለተማሪዎቻቸው ፈተናውን ለመስጠት ዝግጁ ናቸው ተብሏል።
ዶ/ር ማቴዎስ አክለውም፤ ከሞዴል ፈተናው በኋላ የማጠናከሪያ (ቲቶሪያል) ትምህርትና ለጥናት ግብአት የሚውሉ መረጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ፈተናዎች በኦንላይን" ፈተና አስተዳደር ስርአቱ የሚጫንላቸው በመሆኑ ተማሪዎቹ በተፈቀደላቸው "አካውንት" እየገቡ ለጥናት የሚያገለግሉ ሰነዶችን ማንበብ ይችላሉ።
ስለሆነም ትኩረት ሰጥተው በማንበብና ፈተናዎችን በመስራት ራሳቸውን ለዋናው የመውጫ ፈተና ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ዶ/ር ማቴዎስ አሳስበዋል።
በዩኒቨርስቲው በዘንድሮ ዓመት ለተመራቂ ተማሪዎች የሚሰጠው የመውጫ ፈተና የዩኒቨርሲቲው ቀጣይ ህልውና የሚረጋገጥበት ጉዳይ በመሆኑ፤ መላው የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ፈተናው በስኬት ተጠናቆ ተቋማዊ ግባችን እንዲሳካ ሁሉም በትብብር እንዲሰሩ ዶ/ር ማቴዎስ አክለው ጠይቀዋል።
የ"ኦንላይን " ፈተና አስተዳደር ስርዓቱን ካበለጸጉት መምህራን መካከል በዩኒቨርሲቲው የኮምፒተር ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ነጋ ተፈራ በበኩላቸው፤ የ"ኦንላይን " ፈተና አስተዳደር ስርአቱን በዚህ ሁኔታ ወደ ተግባር ለማስገባት እንደተዋረዱ ለኮሌጅ ዲኖች፣ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ መምህራን እና ተማሪዎች ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል።
በዛሬው ዕለት በአምስት ኮሌጆች ስር ከ280 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የሞዴል ፈተናውን በበለፀገው የኦንላይን" ስርአት ለመስጠት ዕቅድ ተይዞ በጠዋቱ መርሃ-ግብር ብቻ ግማሽ ያህሉን መፈተን መቻሉን ተናግረዋል።
የሞዴል ፈተናውን ሲወስዱ ያገኘናቸው ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ የሞዴል ፈተናውን በ"ኦንላይን" ስርአት እንዲፈተኑ መደረጉ በዋናው ፈተና ወቅት ለስርአቱ አዲስ ከመሆን ጋር ተያይዞ ከሚፈጠር የመደናገጥ ችግር ለመታደግ ትልቅ እገዛ እንደሚያረግ ገልጸውልናል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ