የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዛሬ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከሰአት በኋላ ቆይታቸው ልዩ ልዩ የመስክ ምልከታዎችን አካሂደዋል

ዲ.ዩ፦ ግንቦት 25/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ምልከታ እያካሄዱ እንደሆነ ዛሬ ጧት መዘገባችን የሚታወስ ነው።
በጧቱ ክፍለ ጊዜ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲውን የ2015 በጀት ዓመት አበይት ተግባራት የተመለከተ ገለፃ የተደረገላቸው የቋሚ ኮሚቴው አባላት እረፋድ እና ከሰአት በኋላ በነበራቸው ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ውስጥና ከዩኒቨርሲቲው ግቢዎች ውጪ ያሉ የስራ እንቅስቃሴዎችን ተዘዋውረው ቃኝተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በዩኒቨርሲቲው ግቢዎች የተማሪዎች መኝታ ቤት፣ መፀዳጃ ቤት፣ መታጠቢያ ክፍሎች፣ ምግብ ቤት፣ የተማሪዎች ክሊኒክ፣ መማሪያ ክፍሎች እና ቤተመፅሐፍትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ከዚሁም በተጨማሪ በዜሮ ፕላን ፕሮግራም እና የልዩ ፍላጎት ድጋፍ ማዕከልን የስራ እንቅስቃሴዎች የተመለከቱት አባላቱ በአይ.ሲ.ቲ ዘርፍ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የደህንነት እና መረጃ አስተዳደር ስርአት መሰረተ ልማት ስራዎችንም ጎብኝተዋል።
በከሰአት ውሏቸው ደግሞ በይርጋጨፌ በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ በምርምር የለማ የሞዴል አርሶ አደር የቡና ማሳ፣
በዚሁ ይርጋጨፌ ወረዳ ደመርሶ ቀበሌ በማሕበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት የሚለሙ የቡና፣ እንስትና ቅመማቅመም ችግኞች ማፍያ ጣብያንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በዚሁ በደመርሶ ቀበሌ የሚገኝ ለምርምር እና ለማሕበረሰብ አገልግሎት የሚያግዝ የወተት ከብት እርባታ ስራም በቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተጎብኝቷል።
የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በነገው የከሰአት በፊት መርሃግብራቸው የቀሩ የመስክ ምልከታዎችን እንደሚያካሂዱ የተያዘው መርሃግብር ያመላክታል።
ተቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በነገው የከሰአት ውሎ ቆይታቸው ደግሞ ከዩኒቨርሲቲው ከተወጣጡ መምህራን፣ የተማሪ ተወካዮች፣ ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች ኃላፊዎች እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ