የምርምር ሥራዎችን ተመሳስሎት ለመፈተሽ በሚያስችል የ"Turnitin " ሶፍትዌር ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

ዲ.ዩ፡- ግንቦት 29/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፡- የምርምር ስራዎችን ተመሳስሎት ለመፈተሽ (Similarity Checker) በሚረዳ "Turnitin" በተሰኘ ሶፍትዌር ላይ የክህሎት ማዳበሪያ ስልጠና ተሰጠ። ስልጠናው የተሰጠው ለድህረ-ምረቃ አስተማሪዎች፣ ለጆርናል ቦርድ አባላት፣ ለምርምር ጭብጥ መሪዎች እና ለምርምር ካውንስል አባላት ነው።
ስልጠናውን የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምር/ቴክ/ሽግ/ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ከምርምርና ስርፀት ዳይሬክቶሬት እንዲሁም የድህረ-ምረቃ ትምህርት ቤት በጋራ አዘጋጅተውታል።
ዶ/ር ሀብታሙ ተመስገን (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ሶፍትዌሩ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ 14 ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ የገዙት ነው ብለዋል። ሶፍትዌሩ ዓለም ዓቀፍ ቅቡልነት ያለው በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች እና መምህራን በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ አክለው፤ ዩኒቨርሲቲውም እንደ ሀገር 14 ዩኒቨርሲቲዎች “ስብስክራይብ” አድርገው እየተጠቀሙበት ያለውን ይህን ስፍትዌር በርካታ የውጪ ምንዛሪዎችን በማውጣት ጭምር ገዝቶ ጥቅም ላይ ማዋሉ እጅጉን የሚያስመሰግነው ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።
ምስጋናው ለገሰ (ዶ/ር)፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ በበኩላቸው፤ ሶፍትዌሩ ዓለምአቀፍ ደረጃን የጠበቀ እና ታዋቂ እንደሆነ ገልጸው፤ ሶፍትዌሩ ተመሳሳይነትን ከቢሊየኖች ከሚቆጠሩ በይነ መረብ ምንጮች እና የዓለም ዶክመንቶች ጋር በማመሳከር ተመሳሳይነቱ ከየት እንደሆነ የሚገልጽ መሆኑን አስረድተዋል።
ዶ/ር ምስጋናው አይይዘውም ከዚህ ቀደም እንደ ዩኒቨርሲቲ አጋዥ ሶፍትዌር ያልነበረ በመሆኑ ሲቸገሩበት የቆዩበት ጉዳይ እንደነበር አንስተው፤ አሁን ግን ይህ ሶፍትዌር መኖሩ መምህራን እና ተመራማሪዎች የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጌታነህ ሞሱ (ዶ/ር)፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የድህረ-ምረቃ ዲን በበኩላቸው፤ ሶፍትዌሩ በዓለምአቀፍ ደረጃ ጭምር የታወቀ በመሆኑ በርካታ ከበይነ መረብ (ኢንተርኔት) የሚገኙ መረጃዎችን ብቻ በመጠቀም እና በመቅዳት (Copy paste) በማድረግ የሚሰሩ ስራዎችን በማገድ፣ ሰዎች በአዕምሯቸው ብቻ “ኦርጅናል” ስራዎችን እንዲሰሩ እና እንዲያወጡ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ሶፍትዌሩ ከተለያዩ ተቋማት የተሰሩ ምርምሮችን፣ "ኦንላይን" ላይ የሚገኙ ስራዎችን እንዲሁም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተሰሩ ዶክመንቶችን እያመሳከረ የሚቆጣጠር ስለሆነ፤ ጥራት ያላቸው የምርምር ስራዎች እንዲወጡ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
ተክክለኛ እና ወቅታዊ ተቋማዊ መረጃ ለማገኘት
#ቴሌግራም፦ University of the Green Land
ይከታተሉን!
ለጥያቄና አስተያየተዎ
#ኢሜይል፦ pirdir@du.edu.et
ይላኩልን