ለተከታታይ አምስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአቅም ማሻሻያ ፕሮግራም ተማሪዎች ፈተና ተጠናቀቀ

ዲ.ዩ፦ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በአገር አቀፍ ደረጃ የአቅም ማሻሻያ (Remedial) ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለቆዩ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው ፈተና ዛሬ ተጠናቋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲም በዚሁ ፕሮግራም ተቀብሎ የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጣቸው የቆዩትን ተማሪዎች ፈትኗል፤ የፈተናውን ደህንነትና ሚስጥራዊነት በማስጠበቅ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ ከፀጥታ ግብረ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ለ2400 በላይ የተፈጥሮ ሳይንስ እና ከ1600 በላይ የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎች ፈተናውን ሰጥቷል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር )፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፤ እንደ አገር ካጋጠመው ከፍተኛ የውጤች ማሽቆልቆል ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ለተማሪዎች የአቅም ማጎልበቻ መርሐግብር ተዘጋጅቶ ላለፉት አራት ወራት በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ከሰኞ ጀምሮ ፈተናው መሰጠቱን ገልጸዋል።
በነበረው አጠቃላይ ሂደት ውስጥ እንደ ሀገር ባጋጠመው የፈተና ስርቆት ምክንያት ሰኞ ዕለት የተሰጠው ከተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የፊዚክስ እና ከማህበረዊ ሳይንስ ዘርፍ ደግሞ የታሪክ ትምህርት ፈተናዎች ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን፤ በሌሎች የትምህርት መስኮች የተሰጡ ፈተናዎች በአግባቡ እንዲሰጡ ተደርጎ ፈተናዎቹ በሰላም መጠናቀቃቸውን ዶ/ር ችሮታው ገልጸዋል።
ዶ/ር ችሮታው አያይዘው፤ በፈተናው ወቅት የራሳቸው ያልሆነን ውጤት ለማግኘት ሲሉ ያልተገቡ ተግባራትን ሲያከናውኑ የተገኙ 10 ተማሪዎች ከመንግስት በወረደ መመሪያ መሰረት ከፈተናው ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዙ ተደርገው መሰናበታቸውን ገልፀዋል።
አያይዘውም ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ርብርብ ላደረጉት ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ፈተናቸውን አጠናቀው ሲወጡ ያገኘናቸው ተማሪ ቸርነት ማርቆስ እና ተማሪ ናርዶስ ጌታሁን በበኩላቸው፤ ፈተናው በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ በዩኒቨርሲቲው በነበሯቸው የዝግጅት ጊዜያት በመምህራኑ ሲሰጣቸው የቆየው ማጠናከሪያ ትምህርት ለፈተናው ትልቅ እገዛ እንዳደረገላቸው ገልጸውልናል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ