የመጀመሪያ ዙር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መጠናቀቁን ተከትሎ ተማሪዎች ወደ አካባቢዎቻቸው እየተሸኙ ነው

ዲ.ዩ፤ ሐምሌ 21/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፡- የመጀመሪያ ዙር የማህበራዊ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መጠናቀቁን ተከትሎ ተማሪዎች ወደ አካባቢዎቻቸው እየተሸኙ ነው።
በአገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እየተሰጠ የሚገኘው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሶስቱም ጊቢዎች ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ ቆይቶ፤ የመጀመሪያ ዙር ማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ትላንት በነበረ የከሰአት የፈተና መርሃግብር መጠናቀቁ ይታወሳል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የፈተና ማዕከላት፤ ፈተናው በተሰጠባቸው ሶስቱም የዩኒርሲቲው ግቢዎች፤ በኦዳያአ፣ በቀድሞ ዋና ግቢ እና ሐሴዴላ ግቢዎች ከተፈተኑት ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ከቅርብ ርቀት የመጡት ተማሪዎች ወደ አካባቢያቸው የተሸኙ ሲሆን ሌሎችም በተያዘላቸው የጉዞ መርሃ ግብር መሠረት ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ ሽኝት እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
ታምራት በየነ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት እንደገለጹት፤ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እንደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በሰላም ተጠናቆ ተማሪዎች ወደየአካባቢያቸው እየተሸኙ ነው፡፡ ዶ/ር ታምራት አያይዘውም፤ አጠቃላይ በተቋሙ ብሄራዊ ፈተና ለመፈተን ከተመደቡት ከ16 ሺህ 475 በላይ ተማሪዎች አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘው የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ እንደሆነ ገልፀዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ በፈተናው ሂደት፣ በዋናነት ከሲዳማ ክልላዊ መንግስት፣ ከጌዴኦ ዞን እንዲሁም ከሱማሌ ክልል የመጡ ተፈታኞች ዩኒቨርሲቲው ካሉት ካምፓሶች ውስጥ በሶስቱ ፈተናቸውን እንዲውስዱ ተደርገው፤ ካለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ከአንዳንድ ተፈታኞች ከመጠነኛ የስሜት መረበሽ የዘለለ ችግር እንዳልነበር አንስተው እነዚህንም መለስተኛ ሕክምና ተደርጎላቸው መረጋጋት ችለዋል ብለዋል።
ከእናቶች ጋር ተያይዞ መንግስት ባስቀመጠው ማሻሻያ መሠረት እመጫቶችን ጭምር ተቀብለን አስተናግደናል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህም ከ240 በላይ የሚሆኑ የሚያጠቡ እናቶች በፈተና መርሃግብሩ እንደተስተናገዱ ገልፀዋል፡፡ ወደ ዲላ ዩኒቨርስቲ ነፍሰጡር ሆነው ለፈተና ከመጡ ተፈታኞች ውስጥ ሶስት ተፈታኞች በዚሁ በጊቢያችን ውስጥ በሰላም መገላገላቸውንም ነው ዶ/ር ታምራት ያስረዱት።
ዶ/ር ታምራት በየነ፣ በዚህ ፈተና ከአምናው በርካታ ልምዶችን በመውሰድ፤ ከፈተናዎች ኤጀንሲ፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ባለሙዎች፣ ከጉድኝት ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች፣ ቺፎች፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ ፈታኞችና ሌሎችንም አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት አመርቂ ውጤት ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት።
ወ/ሮ ፋንቱ ኤልዶ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ከፍተኛ ባለሙያ እና በሀገር አቀፍ ፈተና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጉድኝት ማዕከል ኃላፊ በበኩላቸው፤ በቅድመ ፈተናው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤታችንና የሚመለከታቸው የትምህርት ማህበረሰብ አካላት ፈተና አስፈፃሚዎች በዩኒቨርሲቲው ቀደም ብለው ለፈተናው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን መሟላታቸውንና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ስራ ቀድመው ሲሰሩ ነበር ብለዋል፡፡
ከተማሪዎች ድልደላ ጋር በተገናኘ የመፈተኛ ቁጥር በማስተካከል በየክፍሉ በመለየት የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች፣ ካፍቴሪያዎች፣ መማሪያ ክፍሎች ለፈተና ምቹ የሚሆንበት ሁኔታ ያመቻቹበት እና እንዲሁም ተማሪዎች ሲመጡ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ስለፈተናው አስፈላጊውን ገለፃ የተሰራበትን ሁኔታ እንዲሁም ከተፈታኞች፣ ከቺፎች፣ ከሱፐርቫይዘሮች ጋር በፈተና ዙሪያ የጋራ መግባባትና ግንዛቤ የተሰጠበት ሁኔታ ጥሩ መሆኑን ወ/ሮ ፋንቱ አንስተዋል፡፡
ወ/ሮ ፋንቱ አክለውም፤ በኦዳያአ ግቢ እኔ የምሰራበት ክላስተር ላይ አምስት ሺህ 122 ተማሪዎች ነው ያሉት፤ እነዚህ ተማሪዎች በአግባቡ ካሉበት ዞንና ወረዳ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት ድጋፍ በማድረግ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በትራንስፖርት መጥተው መፈተኛ ክፍል እንዲገቡ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
አስፈላጊው የተማሪዎች ማደሪያ ክፍል ዝግጅት፣ ለጤና አስፈላጊ የሚበሉ ነገሮች በጥራትና በፍጥነት በማመቻቸት ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሚና ትልቅና የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ መህኑንም ነው ወ/ሮ ፋንቱ የገለፁት።
ከፀጥታ አንፃርና የፈተናው ሚስጥራዊነት እንዲጠብቅ እንደ መንግስትም እንደ ትምህርት ሚኒስቴርም ትልቅ ትኩረት የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምንም አይነት ለፈተናው አስጊ የሆኑ ነገሮች ወደ ግቢ እንዳይገቡ ሁሉም የፀጥታ ሃይሎች ትልቅ የሆነ እገዛ አድርጓል ብለዋል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡን፤ ተፈታኝ ተማሪ ዘሪሁን ኃይሉ እና ተማሪ አለም ሙጂብ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ከአቀባበል ጀምሮ የነበረን ቆይታ መልካም ነበር ብለውናል፡፡ ፈተናው በአገር አቀፍ ደረጃ በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ በራሳችን ጥረትና ልፋት የሚገባንን ውጤት እንድናስመዘግብ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው በማለት፤ ለፈተናው በቂ ዝግጅት በማድረጋቸው የተሻለ ውጤት እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡
ዲላ ዩኒቨርሲቲም ከትላንት ማታ ጀምሮ ተማሪዎቹን ወደየአካባቢያቸው እየሸኘ ሲሆን ጎን ለጎን ለሁለተኛው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና የሚመጡ ተፈታኝ ተማሪዎችን የመቀበሉ ዝግጅት ተጠናቋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ