በታዳሽ ኃይል ልማትና የአቅም ግንባታ ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሄደ

ዲ.ዩ፤ ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በይርጋጨፌ ከተማ ከጌዴኦ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ እማወራዎች በተደራሽ ኃይል ልማትና የአቅም ግንባታ ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል።
መድረኩ በታዳሽ ኃይል ልማትና የአቅም ግንባታ ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር የተካሄደበት ሲሆን፤ በመድረኩ ለተሳተፉ እማወራዎችም በማገዶ ቆጣቢ ምድጃ አሰራርና አጠቃቀም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቶበታል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ጌቱ ታምሩ፣ የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳዳሪ፤ በዓለም ላይ የሚታወቀውን ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ወደምትሰጠው ይርጋጨፌ ወረዳ እንኳን በሰላም መጣችሁ በማለት እንግዶችን ተቀብለዋል።
አያይዘውም፤ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ እንዲሁም ከዞኑ ውሃ፣ ማዕድንና መስኖ ልማት መምሪያ ጋር በመተባበር፣ ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ በተለይ በባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ላይ አርሶአደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ያለውን ስራ አድንቀዋል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና መስኖ ልማት መምሪያ ኃላፊ፤ አቶ ተመስገን ጥላሁን፤ ዞኑ ብዙ ያልተገለጹ ገፅታዎች ያሉት መሆኑን አውስተው፤ እነዚህን ገፅታዎች ለመጠበቅ ደኖችን መንከባከብ የግድ ስለመሆኑ፤ ደኖችን ለመጠበቅ ደግሞ የኢነርጂ አማራጮችን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። ይህንንም ሐሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር መሰል የምክክር መድረኮች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ሲሉ አያይዘው ተናግረዋል።
ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር)፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት በበኩላቸው፤ ይህ በተደራሽ ኃይል ልማትና የአቅም ግንባታ ዙሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገው የምክክር መድረክና ስልጠና፤ ዩኒቨርሲቲው ከኖሮዌይ መንግስት ባሸነፈው ፕሮጀክት በተገኘ ድጋፍ በትብብር የተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዋናነት ሥልጠናው፤ በዞኑ የሚገኙ እናቶችን በተለይ ከዘልማዳዊ የኃይል አጠቃቀም ወደ ተሻሻለ ኃይል ቆጣቢ ወደሆኑ ምድጃዎች፣ ባዮጋዞች እና የፀሐይ ብርሃን ኃይል አመንጭ (ሶላሮች) እንዲሸጋገሩ የማድረግን ሂደት ለማበረታታት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ዶ/ር ሀብታሙ ገለጻ፣ ስልጠናው ከዚህ ቀደም 60 ለሚሆኑ እማወራዎች የተሰጠ እንደሆነ ጠቁመው፤ በቀጣይም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዞኑ እና ከተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች በተደራሽ ኃይል ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ላይ ያተኮረ ጥልቅ የባለሙያዎች ስልጠና እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ አሁን ላይ ከክልሉ ማዕድን ዠና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመሆን በዞኑ ከ150 በላይ የባዮጋዝ ማብላያዎች የገነባ በመሆኑ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ እነዚህ ባዮጋዝ ማብላያዎች በቀጣይ ምሳሌ እንዲሆኑ እና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ባዮጋዝ ማብላያዎችን ላስገነቡ ቤተሰቦች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
አቶ ሰብስቤ አዶላ፣ የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ተወካይ በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው በዞኑ በተለይም በባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ለሚያከናውናቸው ስራዎች ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ከፍተኛ አጋር ሆኖ ለማህበረሰቡ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንዳለ ገልጸዋል።
አክለውም፤ በተለይም በዚህ በጀት አመት ኤጀንሲው በዞኑ ለሚገኙ 150 አባወራዎች የባዮጋዝ ቴክኖጂን ለመገንባት እንደ ክልል ዕቅድ ተይዞ፤ ከሲሚንቶ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ተግባራዊ ለማድረግ አዳጋች በሆነበት ሰዓት፤ ዩኒቨርሲቲው ለ150 አባወራ የሚሆን የሲሚንቶ ዋጋ ሸፍኖ ባዮጋዝ ማብላያዎችን በመገንባት አርሶአደሩን ተጠቃሚ ማድረጉ እጅጉን የሚያስመሰግነው ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በተለይም በባዮጋዝ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ ህብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑ አቶ ሰብስቤ ገልጸዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የመጡት ወ/ሮ ንጋቷ አለሙ እንዲሁም ከወናጎ ወረዳ ወ/ሮ ሀብታም ኪዳኑ በበኩላቸው፤ በማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ስራ ላይ ስልጠና ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸውልናል።
አያይዘውም፤ ስራው በቀላሉ መሰራት የሚቻል ከመሆኑም በላይ በጤና ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ከስልጠናው ጥሩ ግንዛቤ እንዳገኙ ተናግረዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ