ለታካሚዎች የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ጥራት ለማሳደግ የሚያግዝ ስልጠና ተሰጠ

ዲ.ዩ፤ ነሐሴ 01/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል በተለይም ነርሶች ለህሙማን የሚሰጡትን አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል እና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ (Nursing Care Standard) የሚረዳ ሥልጠና መሰጠቱ ተገልጿል።
ስልጠናውን በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል ከጤና ሚኒስቴር ጤና ማሻሻያ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱ ተገልጿል።
ዶ/ር ህይወት ታደሰ፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል የጥራትና ቁጥጥር ማሻሸያ ክፍል ኃላፊ እንደገለፁት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጤና ሚኒስቴር የዛሬ ዓመት ጀምሮ እየተገበረ ያለው የጥራት ማሻሸያ ላይ ለውጥ መኖሩን አስታውሰው፤ ይህ ሥልጠናም የህክምና ሥርዓት ለመለወጥና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል።
እንደ ዶ/ር ህይወት ገለፃ ከሆነ፤ ታካሚዎች ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ በኋላ የሚያገኙት ህክምና በተለይ በነርሶች በኩል የሚደረግላቸው ህክምና ትልቁን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ፤ በሥራ ላይ ያሉ 134 ነርሶችን በሁለት ቡድን ከፍለው ይህንን ስልጠና እንዲወስዱ አድርገዋል።
ዶ/ር ህይወት አክለው፤ ይሁን እንጂ የጤና አገልግሎት በቡድን የሚሰራ አገልግሎት እንደመሆኑ መጠን የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሳካት የስፔሻሊስት ሀኪሞች፣ ጠቅላላ ሀኪሞች፣ ነርሶች፣ ሚድዋይፎች እንዲሁም በየዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ቅንጅት ይፈልጋል ብለዋል።
ስልጠናውን የሰጡት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ "ነርሲንግና ሚድዋይፈሪ" ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ልዑል ደርቤ እና በትምህርት ቤቱ የህጻናት ህክምና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ተስፋዬ እንደገለፁት፤ ስልጠናው በዋናነት ከነርሲንግ ሙያ ጋር በተያያዘ የነርሲንግ ስራ ሂደቶች (Standard of Nursing Care Practice) ላይ ያተኮረ ስልጠና መሆኑን አስገንዝበዋል።
ነርሶች በሙያቸው ከሚኖራቸው አንዱና ዋነኛው ሚና ሆስፒታሉ ውስጥ ለታካሚዎች እንክብካቤ ማድረግ መሆኑን ያነሱት አሰልጣኞቹ፤ ከነዚህ ጋር ተያይዞ ሳይንሳዊ የሆነ፣ አሁን ወቅቱ የሚፈቅደውን ሳይንሳዊ መሳሪያና ምርምር ውጤቶችን ለመጠቀምና ለማዳበር የሚያስችል፣ ሙያ ተኮር የሆነ ሥራ ለመስራት የሚያግዝ ስልጠና ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ስልጠናውን ሲሳተፉ ካገኘናቸው የነርሲንግ ባለሙያዎች መካከል የአጥንት ተኝቶ ህክምና ክፍል ባለሙያ አቶ አማኑኤል ተሾመ እና የቀዶ ጥገና ተኝቶ ህክምና ክፍል አስተባባሪ አቶ ወንድይፍራው ከበደ በበኩላቸው፤ ለታካሚዎች የሚሰጠው አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀና ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ስልጠናው ይረዳል ብለዋል።
ባለሙያዎቹ አክለውም፤ ስልጠናው በተሻለ መነቃቃት ለመስራት፣ ለታካሚዎችም የተሻለ እንክብካቤ ለመስጠትና በየጊዜው ሙያዊ አቅምን ለማሳደግ ይረዳል ሲሉ አስተያየታቸውን ለህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዘጋቢ አጋርተዋል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ