የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጠቅላላ ሆሲፒታል በክረምት የበጎ ፈቃድ ነጻ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው

ዲ.ዩ፤ ነሐሴ 03/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጠቅላላ ሆሲፒታል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍለው መታከም ለማይችሉ የማህበርሰብ ክፍሎች ለተከታታይ ሁለት ሳምንት የሚቆይ ነጻ የጤና ምርመራ፣ የህክምና እና ምክር አገልግሎት እየሰጠ ነው። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከአራት ሺህ ሁለት መቶ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
ዶ/ር ዘመኑ አሸብር፣ የሆስፒታሉ ጥራት ቁጥጥር ኦፊሰር እና የክረምት በጎ ፍቃድ ነጻ ህክምና አገልግሎት አስተባባሪ እንደገለጹት፤ የበጎ ፈቃድ ነጻ የህክምና አገልግሎቱ እስከ ነሐሴ 14/2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም፤ በአግልግሉቱ የጉበት ቫይረስ፣ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርመራ፣ ህክምና እና የምክር አገልግሎት እንዲሁም የደም ልገሳ እንደሚሠጥ አስረድተዋል።
ስለ ህክምና አገልግሎቱ ያስረዱት ዶ/ር ዘመኑ፤ ነጻ ህክምናው በዲላ ከተማ ባሉ ሶስት ጊዜያዊ ማዕከላት እየተሰጠ ሲሆን 14 ስፔሻሊስት ሀኪሞች እና ከ80 በላይ የጤና ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ነው ብለዋል።
የጤና መኮንን ባለሙያ የሆኑት አቤል አፈወርቅ በበኩላቸው፤ በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ከመለየት ባለፈ ህሙማኑ በዘላቂነት ለመከታተል ከጤና መድህን ጋር የማስተሳሰር ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም፤ የሚሰጠው ነጻ ህክምና እና ምርመራ ታካሚዎች ከተጎዱ በኋላ ወደ ጤና ተቋም ከመምጣት ልማድ በማስቀረት ህብረተሰቡ ቀድሞ ስለጤንነቱ ግንዛቤና እውቀት እንዲኖረው ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የነጻ ህክምናውን ሲከታተሉ ካገኘናቸው ተገልጋዮች መካከል፤ አቶ አለማየሁ ሮባ በበኩላቸው፣ የዚህ አይነት የነጻ አገልግሎት በማግኘታቸው በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረው፤ መሰል የበጎ ፈቃድ ዘመቻ በቀጣይነት መኖሩ ለህብረተሰቡ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው አቶ ታሪኩ ኡራጎ እና አማኑኤል ተሾመ በበኩላቸው፤ በየወቅቱ ህብረተሰቡ ደም በመለገስ በደም መፍሰስ ምክንያት እናቶች ላይ ከሚፈጠር አደጋ ማትረፍ እንደሚቻል ገልጸዋል። በቀጣይነትም ደም መለገሳቸውን እንደማያቋርጡም ነው የነገሩን።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ