የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት የ2016  የትምህርት ዘመን ስራን አስጀመረ

ዲ.ዩ፦  መስከረም 07/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኮሚኒት ትምህርት ቤት የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል። 

ብቃትና ጥራት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትምህርት ለአንድ ሀገር ወሳኝ መሆኑን የገለፁት፤  የኮሚኒቲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅና መምህራን ህብረት ሰብሳቢ ዮናታን አየለ(ዶ/ር)፤ ትምህርት ቤቱ ዝግጅቱን አጠናቆ  ወደ ስራ መግባቱን ገልጸው፤ አዲሱን የትምህርት ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አንስተዋል።

ዶ/ር ዮናታን አክለውም፣ ባለፈው አመት እንደ ሀገር ያለው ውጤት አጥጋቢ ባይሆንም የኛ ትምህርት ቤት አፈፃፀም የተሻለ ነበር ሲሉ አንስተዋል። አሁን ከዞን ባለፈ በክልል ደረጃ ከሌሎች ትምህርት ቤቶች ጋር ለመወዳደር እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ዶ/ር ዮናታን ተናግረዋል።

የኮሚኒት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ር/መምህርት የመንዝወርቅ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ካለፉት ጊዜያት አንስቶ በአከፋፈቱ ዙሪያ ሰፊ ስራ መሰራቱን ገልፀው፤ አሁን ለመምህራን  የማስተማሪያ መጽሐፍ  ሙሉ በሙሉ የተዳረሰ እና ቀጣይ ለተማሪዎችም  እንዲዳረስ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ሀይሉ ንጋቱ በበኩላቸው፤ ባለፈው አመት መፃህፍት  ከትምህርት ሚኒስቴር  በሶፍት ኮፒ ብቻ ይላክ እንደነበር  አስታውሰው፤ የታተመው እስከሚደርስ እኛም እያባዛን ለመምራንና ለተማሪዎች የማዳረስ ሥራ እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለጻ ዘንድሮ በተማሪዎች ስነ-ምግባር ላይ የተሻለ ስራ በመስራት የተማሪዎችን ውጤት የተሻለ እንዲሆን እንደሚሰራ  ተናግረዋል።

የቅድመ መደበኛ (ከረ.ጂ) ርዕሰ መምህርት መስከረም በቀለ በበኩላቸው፤ አሁን በተሻለ መልኩ ለስራ ዝግጁነት መኖሩን ገለፀው፤ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከዛሬ መስከረም 07/2016 እንደሚጀመር ባወጣው የትምህርት ዘመን የጊዜ ሰሌዳ ማሳወቁ የሚታወስ ነው።